ኅብረት ለጋዜጠኞች ደህንነት በኢትዮጵያ የፕሬስ ነፃነትን ለማሳደግ ፣ የሚዲያ ባለሙያዎችን መብት ለመጠበቅ እና በመላው ኢትዮጵያ ለጋዜጠኞች ደህንነቱ የተጠበቀ እና አስቻይ ሁኔታን ለመፍጠር የተዘጋጀ ሀገር-አቀፍ የጋዜጠኞች ማህበራት ኅብረት ነው። ጋዜጠኞች ሕዝብን በማንቃት ፣ መልካም አስተዳደር እንዲሰፍን የዜጎች ድምጽ በመሆን ይሰራሉ እንዲሁም በኢትዮጵያ የዴሞክራሲያዊ ማህበረሰብ እንዲጎለብት የሚደረጉ ጥረቶች ውስጥ የጀርባ አጥንት ሆነው ያገለግላሉ። ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ፣ የብዙሃን መገናኝ ባለሙያዎች በሚያጋጥማቸው ዛቻ ፣ ማስፈራሪያ ፣ ሕገወጥ እስር እና የበይነ-መረብ ጥቃቶች ምክንያት ስራቸውን በፍርሃት ለመስራት ይገደዳሉ። በዚሀም ምክንያት ወሳኙን ሚናቸውን ለመወጣት ያላቸው ተነሳሽነትም ሆነ ችሎታ ሲዳከም ይስተዋላል።

እነዚህን አሳሳቢ ፈተናዎች ለመጋፍጥ በዓላማ የሚመሳሰሉ ተቋሞች በጋራ ህብረት ቢፈጥሩ በሚል ኅብረት ለጋዜጠኞች ደህንነት በኢትዮጵያ ተቋቁሟል። ህብረቱም ሰባት የጋዜጠኞች ማኅበራትን በቅንጅት በማሰባሰብ የተመሰረተ ሲሆን ፣ ለጋዜጠኞች ደህንነት እና ክብር ድምጽ እንሚሆን ይታመናል። ይህ የጋራ እንቅስቃሴ የደህንነት ስጋቶችን ለመቅረፍ ከተናጠል ስራዎች በዘለለ በህብረት እና በተቀናጀ አካሄድ የጋዜጠኞችን ችግሮች በመከላከልም ሆነ መፍተሔ በማፈላለግ የተደራጀ የድጋፍ ስርዓት እንዲቋቋም ትልቁን ድርሻ ይወስዳል።

በ ኅብረት ለጋዜጠኞች ደህንነት በኢትዮጵያ መርህ ጋዜጠኞችን መጠበቅ ማለት ዴሞክራሲን መጠበቅ ነው!

ራእይ

በኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ያለፍርሃት ፣ በክብር እና መብታቸው ሙሉ በሙሉ የተጠበቀ ሆኖ ነፃ ፣ ደህንነቱ የተጠበቀ እና አስቻይ የመገናኛ ብዙሃን ዘርፍን መገንባት።

ተልእኮ

የፕሬስ ነፃነትን ማሳደግ ፣ የጋዜጠኞችን ክብር እና ደህንነት ማረጋገጥ እና በጋራ በመቆም ፈጣን ምላሽ ሰጪ ስልቶች ፣ አቅም ግንባታ እና ጾታ-ተኮር እርምጃዎች ላይ በመሰማራት በጋዜጠኞች ማኅበራት መካከል ወንድማማችነትን ማጎልበት።

የኅብረት ለጋዜጠኞች ደህንነት በኢትዮጵያ አባልነት ለሁሉም በሕግ መሰረት የተመዘገቡ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበራት ከሀሳባችንና ከተልእኳችን ጋር ለሚስማማ በሙሉ ተቀባይነት አለው። ለሁሉም በሕግ የተመዘገቡ የጋዜጠኞች ማኅበራት የተመቻቸ ነው። ኅብረቱን በመቀላቀል ማህበራት የሚከተሉትን ጥቅሞች ያገኛሉ፦

  • በብሔራዊ ፣ ክልላዊ እና አለም አቀፍ ደረጃ የውትወታ እና የውክልና የጋራ መድረክ።
  • በስልጠና ፕሮግራሞች ፣ በማሠልጠኛ መመሪያዎች እና ስራዎች እንዲሁም የጋራ ሀብቶች ተደራሽነት።
  • በፈጣን ምላሽ ማሰራጫ ስልቶች እና በጥበቃ አሰራሮች ውስጥ የመሳተፍ እድሎች።
  • በፕሬስ ነፃነት እና በጋዜጠኞች ደህንነት ላይ በቁጥጥር እና ሪፖርት ስርዓቶች ውስጥ መካተት።
  • በጋራ ትብብር እና ልምድ መጋራት በኩል ጠንካራ ግንኙነት እና አጋርነት ጥምረቶች ተሳትፎ።

ይቀላቀሉን እና አባል ይሁኑ

በመላው ኢትዮጵያ የሚገኙ የጋዜጠኞች ማህበራት የኅብረታችን አካል እንዲሆኑ እናበረታታለን። በጋራ በመሆን ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ደህንነቱ የተጠበቀ፣ የበለጠ ነጻ እና ጠንካራ የሚዲያ ሁኔታን መገንባት እንችላለን።

ኅብረት ለጋዜጠኞች ደህንነት በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ባለስልጣን (ሲማድ) በሕግ ተመዝግቦ በምዝገባ ቁጥር 7577 በታህሳስ 14 ፣ 2017 ዓ.ም. ተቋቁሟል። ምዝገባውም ህጋዊነትን ከማረጋገጥ በተጨማሪ ፤ በብሔራዊ ፣ ክልላዊ እና ዓለም አቀፍ ደረጃ ለጋዜጠኞች መብት የመቆም ስራችንን ያጠናክራል።