ህብረት ለጋዜጠኞች ደህንነት በኢትዮጵያ በይፋ ተመረቀ
አዲስ አበባ፡ የተለያዩ የጋዜጠኞች ማኅበራት በጋራ በመሰባሰብ ያቋቋሙት ህብረት ለጋዜጠኞች ደህንነት በኢትዮጵያ በዚህ ሳምንት በኤሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ስራውን በይፋ ጀምሯል። የህብረቱ ምርቃት የመክፈቻውን ጠቅላላ ጉባኤ ተከትሎ የተከናወነ ሲሆን ፣ በቀጣይነትም የጋዜጠኞችን ደህንነት ለመጠበቅ እና በመላ ሀገሪቱ የፕሬስ ነፃነትን ለማስፈን ዓላማ ሰንቆ እንደሚንቀሳቀስ ይጠበቃል።
በጋዜጠኛ የሽዋ ማስረሻ ሰብሳቢነት የሚመራው ጠቅላላ ጉባኤው የአባልነት ጥያቄዎችን ገምግሞ የሶስት ማህበራትን የአባልነት ጥያቄ በማፅደቅ የጥምረቱን ውክልና ለማስፋት ወሳኝ እርምጃ ወስዷል። በዚህም የአማራ ጋዜጠኞች ማህበር፣ የኢትዮጵያ አካል ጉዳተኛ ጋዜጠኞች ማህበር እና የኦሮሚያ ጋዜጠኞች ማህበር ህብረቱን ተቀላቅለዋል።
ሰብሳቢዋ የጉባኤውን ስኬታማነት ሲገልፁ ፣ “ይህ ስብሰባ በኢትዮጵያ ላሉ ሁሉም የሚዲያ ባለሙያዎች ምቹ ሁኔታን ለመፍጠር ያደረግነውን የጋራ ውሳኔ ያጠናክራል።” አባላቱንም በህብረት እና የተቀናጀ ስልታዊ መንገድ ለመጓዝ ላደረጉት ከፍተኛ ተሳትፎ አመስግነዋል።
በርካታ የሲቪክ ማህበራት፣ የሚዲያ ተወካዮች፣ አጋር ተቋማት፣ ምሁራን እና ባለድርሻ አካላት በተገኙበት የህብረቱ የምርቃት ፕሮግራም በድምቀት የተከናወነ ሲሆን ፤ የህብረቱ አባላት እስካሁን በነበረው ሂደቱት የኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር የተጫወተውን ሚና በጋራ አመስግነው ከ IMS በኩል ለተደረገውም ድጋፍ አድናቆታቸውን ሰንዝረዋል።
የዚህ ዓይነቱ ህብረት አስፈላጊነት በተሰብሳቢዎች አጽንዖት ተሰጥቶታል። በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነት ትምህርት ቤት ረዳት ፕሮፌሰር የሆኑት አብዲሳ ዘርአይ የምስረታውን አስፈላጊነት ላይ ትኩረት በማድረግ "በመላው ኢትዮጵያ ጋዜጠኞችን ለመጠበቅ የሚደረገውን ልዩ ልዩ ጥረቶች ለማጠናከር እና የስራ ድግግሞሽን ለማስወገድ ፤ በተለይም ዓለም አቀፋዊ የሚዲያ ሥነ-ምህዳር ከፍተኛ አደጋዎች በተጋረጠበት በዚህ ወቅት ፤ እና የተቀናጀ ብሔራዊ ምላሽ ለመስጠት የዚህ ህብረት መመስረት በጣም ወሳኝ ነው።"
የህብረቱ ምርቃት የተከናወነው ፣ የጋዜጠኞችን ደህንነት ለመጠበቅ ያለመ እና ትኩረቱንም በግጭት ቀጠናዎች በሚሰሩ ጋጋዜጠኞች ላይ ያተኮረ የሁለት ቀናት የአሰልጣኞች ስልጠና ፕሮግራም በተሳካ ሁኔታ መፈጸሙን ተከትሎ ነው። ስልጠናው በኢትዮጵያ አርታኢያን ማህበር የተዘጋጀ ሲሆን ፣ በ IMS ፣ FCDO እና NORAD ድጋፍ ጋር የተተገበረ ነው። ስልጠናው የጋዜጠኞችን የአካል፣የህግ፣ዲጂታል እና አእምሯዊ ደህንነትን በተመለከተ አቅም ግንባታ ፣ ጥበቃ እና አፋጣኝ ምላሽ መስጠት የሚያስችሉ መመሪያዎች በአማርኛ ፣ በኦሮሚኛ እና በእንግሊዝኛ ታትመው የተሰራጩበት ነበር።
ህብረቱ በቀጣይ ባለው መደበኛ ስራው፣ በመላው ኢትዮጵያ የጋዜጠኞችን ደህንነት እና ሙያዊ ታማኝነትን በማስተዋወቅ የጥብቅና፣ ድጋፍ እና ስትራቴጂ ማእከላዊ አስተባባሪ እንደሚሆን ይጠበቃል።